ሀገር አቀፍ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 9/2011)በቀጣዩ ወር ሊካሄድ የነበረው 4ኛው ሀገር ዐቀፍ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም መወሰኑ ተነገረ።

ሪፖርተር እንደዘገበው  በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የሚመራው የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ  ኮሚሽን ውሳኔውን ያሳለፈው ከትናንት በስትያ  ቅዳሜ ዕለት በተጠራ ስብሰባ ብዙ ክርክር ከተካሄደበት በኋላ ነው፡፡

በዚህ መሠረት ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ የቆጠራ ቁሶችን ወደ ክልሎች ማሰራጨቱን እንዲያቋርጥ፤ ያሰራጫቸውንም ወደ ማዕከሉ እንዲመልስ ታዟል ተብሏል ፡፡

የደቡብ ክልል በጸጥታ ችግር ምክንያት ቆጠራውን ለማድረግ እንደማይችል ማሳወቁ ይታወሳል፡፡

የአማራ ክልል እና ሌሎችም ክልሎች  ቆጠራውን ለማካሄድ ዝግጅት እያደረጉ ነበር ። ይህም ሆኖ ግን የቆጠራ ቁሶችን እስካሁን የተረከበው  ትግራይ ክልል ብቻ ነው ተብሏል፡፡

ሃገር አቀፍ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ በሕገመንግስቱ መሰረት በየ10 ዓመት መካሄድ እንደሚኖርበት ይደነግጋል።

በዚሁም መሰረት በ1999 ዓም የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ከተካሄደ በኋላ በ2009 መካሄድ ቢኖርበትም በኢትዮጵያ በተፈጠረው ፖለቲካዊ አለመረጋጋትና ይሕንኑ ተክትሎ በተፈጠሩ ግጭቶች ሳቢያ ከሁለት ጊዜ በላይ ተራዝሟል።

አሁንም በኢትዮጵያ ባለው የፖለቲካ አለመረጋጋት ሳቢያ 4ኛው አገር ዐቀፍ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ እንዲራዘም ሲጠይቅ ቢቆይም በቀጣዩ ወር እንደሚካሄድ መንግስት ሲያሳውቅ ቆይቷል።

እንደ ሪፖርተር ዘገባ መንግስት እንደገና ሀሳቡን በመቀየር 4ኛው አገር ዐቀፍ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም ኮሚሽኑ ወስኗል።

The post ሀገር አቀፍ የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ ላልተወሰነ ጊዜ ተራዘመ appeared first on ESAT Amharic.


Source: ESAT