በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሰውና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ተወገዘ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 1/2011)የአማራ ክልላዊ መንግሥት በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሰውና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት አወገዘ፡፡

በአካባቢው በተከሰተው ግጭቱ ሳቢያ መጠኑ ባልታወቀ ሁኔታ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱም ታውቋል።

ሁለት ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ ወድመዋል በተባለበት በዚሁ ግጭት ፋብሪካም ተቃጥሏል። 55 ከብቶችም ሞተዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን ደምቢያ ወረዳ በተፈጠረው ግጭት እስካሁን ባለው ሁኔታ የሟቾች ቁጥር በይፋ አልተገለጸም።

በርካታ ቤቶች ተቃጥለው ከ50 በላይ የቤት እንስስሳት መሞታቸውም ተግሯል።

የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አሰማኸኝ አስረስ በደምቢያ ወረዳ እየተስተዋለ ባለው አለመረጋጋት በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የአማራ ክልል መንግሥት ማውገዙን ተናግረዋል፡፡

ግጭቱ ሁለቱንም ሕዝቦች የማይወክል መሆኑ በተጨባጭ ማስረጃ መረጋገጡንም ነው ያስታወቁት፡፡

“በማዕከላዊ ጎንደርና በአካባቢው የተነሳውን በአማራና በቅማንት ተወላጆች መካከል የተፈጠረ አይደለም። ቅማንት ችግር ሲገጥመው የሚያስጠጋው አማራው ነው አማራው ችግር ሲደርስበት የሚደርስለት ቅማንቱ ነው”ብለዋልየአማራ ክልል የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኽኝ አስረስ

ከጉዳዩ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው በሚል የተያዙ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውንና የእሥር ማዘዣ የወጣባቸው እንዳሉም አቶ አሰማኸኝ ተናግረዋል፡፡

እንደ ዋና ዳይሬክተሩ መረጃ ግጭቱ ዳግም ያገረሸበት ምክንያት አካባቢውን ለማረጋጋት ተሰማርቶ የነበረው 24ኛ ክፍለ ጦር ወጥቶ 33ኛ ክፍለ ጦር ለግዳጅ እየገባ በነበረበት ጊዜ ነው ብለዋል።

ጥር 24/2011 ዓ.ም መንግሥት ‹‹የተደራጁ ቡድኖች›› ያላቸው አካላት በጸጥታ አካላት ላይ ጥቃት በማድረሳቸው ነውም ተብሏል፡፡

 

The post በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሰውና በንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ተወገዘ appeared first on ESAT Amharic.


Source: ESAT