በምስራቅ ወለጋ አንድ ሻለቃን ጨምሮ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተገደሉ

(ኢሳት ዲሲ–ሚያዚያ 21/2011) በምስራቅ ወለጋ ሻምቦ አካባቢ ከኦነግ ጋር በተካሄደ ውጊያ አንድ ሻለቃን ጨምሮ የመከላከያ ሰራዊት አባላት መገደላቸው ተነገረ።

በውጊያው ሻለቃ ይበሉ ጌታቸው የተባለ ነባር የሰራዊቱ አባል በኦነግ ከተገደለ በኋላ አስከሬኑ ለቤተሰቦቹ መሰጠቱ ታውቋል።

በውጊያው ሌሎች የሰራዊቱ አባላት መገደላቸውንም አስከሬኑን ያመጡት ኮሎኔል መግለጻቸውንም የሻለቃው ቤተሰቦች ለኢሳት ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት ከኦነግ ታጣቂዎች ጋር በምስራቅ ወለጋ ውጊያ እንደሚያካሂዱ የአካባቢው ምንጮች ይገልጻሉ።

የኦነግ ታጣቂዎች ሕዝቡን ተገን በማድረግ በሚፈጽሙት ጥቃትም የመከላከያ ሰራዊት አባላት እየተገደሉ መሆናቸውን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

ባለፈው ሃሙስ በምስራቅ ወለጋ ሻምቦ አካባቢ ከኦነግ ጋር በተካሄደ ውጊያ ሻለቃ ይበሉ ጌታቸው የሚባል የሰራዊቱ አባል መገደሉ እንደተነገራቸውና አስከሬኑ እንደመጣላቸው ቤተሰቦቹ ለኢሳት ገልጸዋል።

ከቤተሰቦቹ መካከል ታደሰ አለሙ የተባለ ወጣት እንደገለጸልን ሟቹ ሻለቃ ይበሉ ጌታቸው በሰራዊቱ ውስጥ ከ21 አመታት በላይ አገልግሏል።

በሱዳንና ሩዋንዳ ሰላም የማስከበር ተልዕኮ ግዳጁን የተወጣው ሻለቃ ይበሉ ጌታቸው በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜም ዋጋ ከከፈሉት የሰራዊቱ አባላት መካከል እንደነበርም ገልጿል።

ይህም ሆኖ ግን ሻለቃ ይበሉ ጌታቸው የከፈለው መስዋዕትነት ዋጋ ሳይሰጠው አስከሬኑን እንዳናይ ተደርገናል።አስከሬኑንም ወደ ፍኖተ ሰላም ከተማ ያመጡት 3 የሰራዊቱ አባላት 5ሺ ብር ከጓደኞቹ ተዋቶ ወደ ቤተሰብ ማድረሳቸውንም ገልጿል።

ሻለቃ ይበሉ ጌታቸው ግማሽ እድሜውን ለሃገሩ ከፍሎ በመንግስት በኩል ትኩረት መነፈጉ የሃገሪቱን ውለታ ቢስነት ያሳያልም ነው ያለው።

ሻለቃ ይበሉ ጌታቸው ባለትዳርና የአንድ ወንድ ልጅ አባት መሆኑን እንዲሁም አንድ አረጋዊት እናት እንዳሉትም ቤተሰቦቹ ገልጸዋል።

በመስራቅ ወለጋ ሻምቡ አካባቢ በነበረው ውጊያ ከመከላከያ ሰራዊት አባላት የተገደሉ እንዳሉ ቢታወቅም ከኦነግ በኩል ስለደረሰው ጉዳት ግን የተገለጸ ነገር የለም።

 

 

The post በምስራቅ ወለጋ አንድ ሻለቃን ጨምሮ የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተገደሉ appeared first on ESAT Amharic.


Source: ESAT