በአማራ ክልል ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 90ሺ ደረሰ

(ኢሳት ዲሲ–የካቲት 7/2011)በአማራ ክልል ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎ ቁጥር 90ሺ ያህል መድረሱን የክልሉ የኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ገለጹ።

ተፈናቃዮቹ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው ከመምጣታቸውና ያረፉበትም ቦታ የተለያየ መሆኑ ደግሞ የተፈናቃዮቹ ቁጥር ከዚህም በላይ ሊያሻቅብ ይችላል ብለዋል የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ አሰማህኝ አስረስ ከኢሳት ጋር ባደረጉት ቆይታ።

ለተፈናቃዮቹ የክልሉና የፌደራል መንግስት በጋራ ድጋፍ ቢያደርጉም በቂ ሊሆን አልቻለም ብለዋል።

ስለዚህ ተጨማሪ እርዳታ ለማግኘትና ተፈናቃዮቹን በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ወደ ቀያቸው ለመመለስ የድጋፍ ማሰባሰቢያ የባንክ ሒሳብ መከፈቱንም አስታውቀዋል።

ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉት የአማራ ተወላጆች ቁጥር ባለፈው ህዳር ከ15ሸና ከ20 ሺ አይበልጥም ነበር።

እነዚህ የክልሉ ተወላጆች የተፈናቀሉት  ከቤንሻንጉል፣ከአፋር፣ከትግራይ፣ከኦሮሚያ፣ከሶማሌና ከጅቡቲ ነበር ይላሉ የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሃላፊው አቶ አሰማኽኝ አስረስ።

እነዚህን ተፈናቃዮች ለማገዝ ደሞ ክልሉ በጀት ከመመደብ ጀምሮ ግብረ ሃይል አቋቁሙ ድጋፍ አስከማድረግ ድረስ ሲሰራ ቆይቷል።

ነገር ግን በክልሉ ያለው ግጭት እየተባባሰ መምጣቱ ግን የተፈናቃዮቹ ቁጥር እንዲያሻቅብ አድርጎታል ይላሉ አቶ አሰማህኝ።

ከሁሉ ተፈናቃዮች ደግሞ ከምዕራብና ከማዕከላዊ ጎንደር የተፈናቀል ወገኖች ሁኔታ አስከፊ ነው ይላሉ።–መኖሪያቸው በሙሉ መውደሙን በመግለጽ

ለእነዚህ ተፈናቃዮች አስቸኳይ እርዳታ በማድረግ ረገድ የፌደራሉ መንግስት ድጋፍ አልተለየንም ብለዋል።

የትግራይ ክልላዊ መንግስትም ድጎማ በማድረግ ድጋፉን አድርጓል።ለተፈናቀሉት ወገኖች የ7 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል ብለዋል።

ይሁን እንጂ የተፈናቃዮቹ ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ መምጣት ክልሉ የግዴታ የሌሎችን ድጋፍ ለመጠየቅ ተገዷል ይላሉ።

በገንዘብ ደረጃ ምን ያህል ያስፈልጋል የሚለው ገና አልተሰራም ያሉት ሃላፊው በእርግጠኝነት ተፈናቃዮቹን ለማቋቋም በቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ተፈናቃዮቹ ለመቋቋም በክልሉ ብቻ ሳይሆን በፌደራል መንግስት ደረጃም የታሰበ ስራ አለ ብለዋል።

በክልሉ እየቀነሰ ሳይሆን እየጨመረ የመጣውን ችግር ዳግም እንዳይፈጠር እቅድ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ነው የገለጹት።

በክልሉ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮች በተወላጆቹ መካከል የተፈጠረ አይደለም።በህዝቡ መካከል ምንም አይነት ችግር የለም።በማንኛውም ችግር ውስጥ አንዱ ለአንዱ ሲቆም ይታያል እንጂ ችግር ሲፈጥር አይታይም ብለዋል።

ነገር ግን በሕዝቡ ውስጥ ችግር እንዲፈጠር የሚያደርጉ አካላት አሉ።–እነዚህ ደግሞ ለህግ ማቅረብ ጊዜ የማይሰጠው ተግባር ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አቶ አሰማህኝ ከክልሉ አቅም በላይ የሆኑ ችግሮች መኖራቸውን ግን ሳይናገሩ አላለፉም።

 

 

The post በአማራ ክልል ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 90ሺ ደረሰ appeared first on ESAT Amharic.


Source: ESAT