በጀርመን የሃገሪቱ ፖለቲከኞችና የሃገሪቱ መሪ መረጃ ተሰረቀ

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 26/2011)በጀርመን የኢንተርኔት መረጃ ጠላፊዎች ከመቶ በሚበልጡ የሃገሪቱ ፖለቲከኞችና በሃገሪቱ መሪ ላይ ጭምር የመረጃ ስርቆት መፈጸማቸው ተሰማ።

የኢንተርኔት መረጃ ጠላፊዎቹ የጀርመኗ መራሂተ መንግስት አንጌላ ሜርክልን የግል መረጃ ጭምር ከሰረቁ በኋላ በኢንተርኔት ማሰራጨታቸው ተሰምቷል።

ጠላፊዎቹ የጋዜጠኞችንና የኪነጥበብ ሰዎችን መረጃም ሰርቀው ማውጣታቸውም ታውቋል።

በጀርመን ዛሬ በደረሰው የዚህ የኢንተርኔት ጥቃት ከመቶ የሚበልጡት ፖለቲከኞች፣ ጋዜጠኞችና የኪነጥበብ ሰዎች፣ የግል መረጃዎች፣ የገንዘብ ሚስጥሮች፣ በግል የተጻጻፏቸው መልዕክቶች ጭምር ተሰርቀው በቲውተር ገጽ ላይ ተበትነዋል።

ድርጊቱን የፈጸመው ማን እንደሆነ ባይታወቅም አክራሪ የቀኝ ክንፍ የጀርመን ፖለቲከኞች በጥቃቱ አልተካተቱም።

የጀርመን የፍትህ ሚኒስትር ካትሪና ባርሊ ጥቃቱ አደገኛ እንደሆነ ገልጸዋል።

ስለደረሰው ጉዳት መጠን ባይዘረዝሩም በዲሞክራሲያችንና በተቋማታችን ላይ የተቃጣ ነው ሲሉም አክለዋል።

የጀርመን የፌደራል የኢንፎርሜሽን ደህንነት ተቋም BSI በጉዳዩ ላይ ምርመራ መጀመሩን የገለጸ ሲሆን በጥቃቱ የሃገሪቱ መሪ ጭምር ሰለባ ቢሆኑም የሃገሪቱ የመንግስት የኢንተርኔት ኔትወርክ ግን ከአደጋ ነጻ መሆኑ ተረጋግጧል።

የመንግስት ኔትወርክ ከአደጋው ነጻ ቢሆንም የሃገሪቱ መሪ አንጌላ ሜርክል እጅግ ወሳኝ ምስጢሮች ጭምር ተሰርቀው መሰራጨታቸውን የመንግስት ቃል አቀባይ ገልጿል።

ሆኖም ከፍተኛ የፖለቲካ አደጋ የሚያስከትሉ መረጃዎች አለመውጣታቸውም ተመልክቷል።

ጥቃቱን ማን እንዳደረሰው የታወቀ ነገር የለም፣ ሃላፊነቱን የወሰደ አካልም አልተገኘም።ሆኖም የቀኝ ክንፍ አክራሪ ጀርመኖችና ሩሲያ በጠለፋው ተጠርጥረዋል።

The post በጀርመን የሃገሪቱ ፖለቲከኞችና የሃገሪቱ መሪ መረጃ ተሰረቀ appeared first on ESAT Amharic.

Source: ESAT