በጎፋ ዞን አላግባብ የሚታሰሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ

(ኢሳት ዲሲ–መጋቢት 18/2011)በጎፋ ዞን አላግባብ የሚታሰሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ገለጹ።

ባለፉት ሶስት ቀናት ብቻ በአካባቢው ፖሊስና በዞኑ አስተዳደር የማንነት ጥያቄ አንስታችኋል በሚል የታሰሩ ዜጎች ቁጥር ከ30 በላይ መድረሱን ለኢሳት የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

ኢሳት በጉዳዩ ላይ የዞኑን አስተዳዳሪ ለማነጋገር ሙከራ አድርጎ ነበር አስተዳዳሪው ስብሰባ ላይ ነኝ የሚል መልስ በመስጠታቸው ይሄ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ አስተዳዳሪውን አግኝቶ ማነጋገር አልቻለም።

በጎፋ ዞን ካለምክንያት ዜጎችን ማሰር እንግዳ ነገር አይደለም ይላሉ የዞኑ ነዋሪዎች ለኢሳት።

እነሱ እንደሚሉት ከሆነ የአመራሮችን ፎቶ አቃጥላችኋል በሚል በእርስ ቤት የሚንገላቱ ዜጎች ቁጥር ወደ 50 ተጠግቷል።

ይሄንንም ኢሳት በቅርቡ ለሕዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

የእነዚህ እስረኞች ጉዳይ መፍትሄ ባላገኘበትና የፍትህ ስርአቱ በአግባቡ ሊያስተናግዳቸው ባልቻለበት ሁኔታ ውስጥ ሰሞኑን ደግሞ የማንነት ጥያቄ አንስታችኋል በሚል የሚታሰሩ ዜጎች ቁጥር እየተበራከተ መቷል ይላሉ ነዋሪዎቹ።

ምናልባትም ይላሉ አንደኛው ነዋሪ የማንነትም ጉዳይ ሳይሆን የማካለሉ ጥያቄ ለእስራቱ ምክንያት ሊሆን ይችላል።

እንኳን ጓደኞቼ አይደሉም እኔም ለመታሰር እየተፈለኩ ነው ብለዋል ኢሳት ካነጋገራቸው ነዋሪዎች አንዱ።

ኢሳት ከሰአታት ቆይታ በኋላ መረጃ ለማሰባሰብ ወደ አካባቢው በደወለበት ወቅት መረጃውን ያደረሱትና ልታሰር እየተፈለኩ ነው ያሉት ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለማወቅ ችሏል።

በአካባቢው በነዋሪዎች ላይ የሚደረገው አላግባብ እስርን የሚፈጽመው የአካባቢው ፖሊስና የዞኑ አስተዳደር በትብብር መሆኑንም ነዋሪዎቹ ይናገራሉ።

እስካሁንም የአካባቢው ነዋሪዎችን የማሰሩ ተግባር መቀጠሉንና ቁጥራቸውም ከ30 በላይ መድረሱን ይናገራሉ።

ነዋሪዎቹ እንደሚሉት ከሆነም የአካባቢው ነዋሪዎች የሚታሰሩበትን ምክንያት ለመጠየቅ ቢፈልጉም መብቱ የላቸውም።

እስረኞቹ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጋቸውን ነገር ግን በችሎቱ የቀረበባቸው ክስ ጭራሽ ከታሳሪዎቹ ጋር የማይገናኝና አዲስ መሆኑን ነው የሚናገሩት።

ኢሳት ስለጉዳዩ ለማጣራት ወደ ጎፋ ዞን አስተዳዳሪ አቶ አዱኛ አክሊሉ ስልክ ቢደውልም ስብሰባ ላይ ነኝ የሚል መልስ በመስጠታቸው ምላሽ ማግኘት አልቻለም።

ይሄ ዜና እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስም ኢሳት አስተዳዳሪውን አግኝቶ ለማነጋገር አልቻለም።

 

 

 

The post በጎፋ ዞን አላግባብ የሚታሰሩ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ ተገለጸ appeared first on ESAT Amharic.


Source: ESAT