ኦነግ የአየር ድብደባ ተፈጽሞብኛል አለ

(ኢሳት ዲሲ–ጥር 10/2011) በምዕራብ ኦሮሚያ ምንም አይነት የአየር ድብደባ አለተፈጸመም ሲል የጠቅላይ ሚኒስትር ያወጣውን መግለጫ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) አስተባበለ።

በቄለም ወለጋ ዞን ለሁለት ተከታታይ ቀናት የአየር ድብደባ ተፈጽሟል ሲል ኦነግ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የኢትዮጵያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በትናንትናው ዕለት  በቃል-አቀባዩ ብልለኒ ስዩም በኩል በምዕራብ ኦሮሚያ ጦሩ ያካሄደዉን የአየር ድብደባ  የለም በሚል መግለጫ አውጥቶ ነበር።

ይህም ሆኖ ግን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር(ኦነግ) መግለጫው እጅጉን ከእዉነት የራቀ ነዉ ሲል የማስተባበያ መግለጫ አውጥቶታል።

ይህ የአየር ድብደባ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ጥር 4 እና ጥር 5 /2011 ዓም በቄለም ወለጋ ዞን በጊዳሚ ወረዳ በቄለም ከተማና አካባቢዋ በሶስት የተለያዩ ቦታዎች ለይ ተካሂዷል ብሏል።

በዚህ ደረጃ የተካሄደዉን የአየር ድብደባ ለመካድ መሞከር  “ግመል ሰርቆ አጎምብሶ” እንደመሄድ ይቆጠራል ብሏል ኦነግ ባወጣው መግለጫ።

ከዚሁ የአየር ድብደባ በተጨማሪም የኢሕአዴግ እግረኛ ጦር ሠራዊት በዚሁ አካባቢ ሰላማዊዉን ሕዝብ በመግደል፣ መኖሪያ ቤቶቹን በማቃጠል፣ ንግድ ቤቶቹን በማፈራረስና ንብረት በመዝረፍ እንዲሁም ሰዎችን በጅምላ በማሰርና በማሰቃየት እኩይ ድርጊቶች ፈጽሟል ሲል ክስ አቅርቧል።

እንደ ኦነግ መግለጫ በጊዳሚ ወረዳ ዉስጥ በአየር ሃይልና በእግረኛ ጦር በተካሄደዉ በዚህ ጥቃት እስካሁን  የሰባት  ሰላማዊ  ዜጎች ሕይወት አልፏል፣ 8  መኖሪያ ቤቶች በእሳት ሲጋዩ 20 የንግድ ቤቶችም በኢሕአዴግ ወታደሮች ተዘርፈው ፈራርሰዋል ነው ያለው።

እነዚህ በጊዳሚ ወረዳ ዉስጥ የአየር ጥቃቱ በተካሄደበት ኣካባቢ ብቻ የተፈጸሙ ናቸዉ።

ግድያና ጦርነት እየተካሄደባቸዉ ባሉት በአራቱ የወለጋ ዞኖችም በነዚሁ የኢሕአዴግ ወታደሮች የተገደሉት ሰላማዊ ሰዎች፣ የተቃጠሉ ቤቶች፣ የተዘረፉና የወደሙ ንብረቶች በርካታ ሲሆኑ ለወደፊቱ ተጣርተው ይቀርባሉም ብሏል መግለጫው ።

 

 

The post ኦነግ የአየር ድብደባ ተፈጽሞብኛል አለ appeared first on ESAT Amharic.


Source: ESAT