የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ በመጪው ሚያዚያ ሊካሄድ ነው

(ኢሳት ዲሲ–ታህሳስ 19/2011)በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት የነበረው የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ በመጪው ሚያዚያ ሊካሄድ መሆኑን ኤጀንሲው አስታወቀ።

የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው የሕዝብና የቤት ቆጠራን ለማካሄድ አንድ ነጥብ ሰባት ቢሊየን ብር እስካሁን ድረስ ወጭ ተደርጓል።

የሕዝብና የቤት ቆጠራው በሕገ መንግስቱ መሰረት በየ10 አመቱ መካሄድ ቢኖርበትም በኢትዮጵያ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት መካሄድ ከነበረበት ጊዜ ሁለት አመት አልፎታል።

የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ እንዳስታወቀው የሕዝብና የቤት ቆጠራውን ባለፈው አመት ሕዳር ለማካሄድ ታቅዶ ሁኔታዎች ባለመመቻቸታቸው ለመጋቢት ተቀጥሮ ይህም ሳይሳካ ቀርቷል።

ይህም የሆነው በሃገሪቱ ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት የፈጠረው ችግር ነው ብሏል።

በኢትዮጵያ ታሪክ ለ4ኛ ጊዜ ይካሄዳል የተባለው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ታዲያ ከ2 አመታት መዘግየት በኋላ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 14/2011 እንደሚካሄድ የማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ አስታውቋል።

ይህም ሆኖ ግን አስቸጋሪ ነገር ከተፈጠረና ቅድመ ዝግጅቱ ካልተጠናቀቀ ቆጠራው ሊራዘም እንደሚችል በኤጀንሲው የኢንፎርሜሽንና የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ሰፊ ገመዲ ገልጸዋል።

እንደ አቶ ሰፊ ገለጻ እስካሁን ባለው ቅድመ ዝግጅት የሕዝብና የቤት ቆጠራ ካርታ እንዲሁም የጥያቄና የመረጃ ግምገማ ሰነዶች ተዘጋጅተዋል።

ለዚሁም 150ሺ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ካርታ ለገጠርና ለከተሞች ተዘጋጅቷል ነው ያሉት እስካሁን ለስራው የወጣው ገንዘብ ደግሞ 1 ነጥብ 7 ቢሊየን ደርሷል ብለዋል።

ስራውን ለማከናወን ለሚያስፈልገው የሰው ሃይል ደግሞ 148ሺ ቆጣሪዎችና 37ሺ ተቆጣጣሪዎች እንደሚያስፈጽሙት ሃላፊው ገልጸዋል።

ይህን ስራ ለመስራት የቴክኒክ ብቃት ባላቸው የ1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪዎች ላይ ምልመላው ትኩረት እንደሚያደርግም ነው የገለጹት።

ቆጠራው የሚካሄደውም 663 ሚሊየን ብር በታገዙ 180ሺ ታብሌቶች እንደሚሆንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ፓርላማ ባለፈው ጊዜ ብሔራዊ የሕዝብና የቤት ቆጠራ ኮሚሽን አቋቁሟል።

በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ኮሚሽነርነት የሚመራው ይህው ተቋም 20 አባላት ያሉት ሲሆን በስሩም ዘጠኝ ሚኒስትሮችና ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እንዲሁም ከክልል የተውጣጡ ተወካዮችን አካቷል።

የሕዝብና የቤቶች ቆጠራው በመጭው ሚያዚያ መጀመሪያ ላይ ይካሄዳል ቢባልም በአሁኑ ጊዜ ባለው የሃገሪቱ ሁኔታ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።

ምርጫው ካልተላለፈም ቆጠራውን ለማካሄድ አስቸጋሪ ሊያደርገው ይችላል ተብሏል።

በኢትዮጵያ በስራ ላይ ባለው ሕገ መንግስት የሕዝብና ቤት ቆጠራው በየ10 አመቱ መካሄድ ነበረበት።

 

The post የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ በመጪው ሚያዚያ ሊካሄድ ነው appeared first on ESAT Amharic.

Source: ESAT